1/2የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በሩብ ዓመቱ ባካሄደው ጥብቅ የላብራቶሪ ምርመራ ከደረጃ በታች ሆነው ያገኛቸውን አንድ የእንስሳት መድኃኒት እና ሦስት ክትባቶች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ማድረጉን ገለጸ።
የባለስልጣኑ የእንስሳት መድኃኒት ሬጉላተሪ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሰለሞን ከበደ እንደገለጹት፤ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ፣ ከሀገር በሚወጡ እንስሳት እና የእንስሳት ውጤቶች ላይ የጥራት እና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ በሰፊው እየተሰራ ነው።
በእንስሳት መኖ እና መድኃኒት ላይ የጥራት ችግር እንደሚነሳ የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን፥ አንዳንድ የሚፈለጉ መድኃኒቶች በገበያ ላይ ያለመገኘት ችግሮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ዶ/ር ሰለሞን ከበደ በዝርዝር ምን አሉ?
"መድኃኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ኬላ ላይ ደህንነታቸውን በላብራቶሪ በማረጋገጥ የጥራት ችግር ያለባቸው እንዲወገዱ እያደረግን ነው።
በባለፈው ዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት የእንስሳት መድኃኒት የጥራት ችግር ያለበት በመሆኑ ምክንያት እንዲወገድ እና ወደ መጣበት ሀገር እንዲመለስ ተደርጓል።
በተያዘው በጀት ዓመት በሩብ ዓመት ወደ 114 መድኃኒቶችን እና ክትባቶችን በመርምር አንድ መድኃኒት እና ሦስት ክትባቶች ከደረጃ በታች መሆናቸው ተረጋግጦ አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ ተደርጓል።
የእንስሳት መድኃኒትን አቅርቦት አማራጮችን ከማሻሻል አንፃር በጣም ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው። በገበያ ላይ በብዛት የማይገኙ መድኃኒቶችን በመመዝገብ ወደ ሀገር ውስጥ እንድገቡ እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አገልግሎቶቹ በመሶብ አንድ ማዕከል፣ በኢ-ሰርቪስ እና በአንድ መስኮት እየተሰጡ ነው። አሰራራችንን በዲጂታል በማድረጋችን የመድኃኒት አማራጮች እንዲኖሩ አድርጓል" ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ያለ እንስሳት ሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ የሚሰጡና በመድኃኒት ማዝዣ የሚታደሉ መድኃኒቶችን ለመለየት የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ በፍትሕ ሚኒስቴር መጽደቁን ጠቁመዋል።
የመድኃኒት አጠቃቀምን ለመቀነስና በሽታ እንዳይከሰት ቅድመ-መከላከል ላይ ያተኮረ የ'አንቲ ማይክሮባይል ስዋርዲሺፕ' ማኑዋል ከግብርና ሚኒስቴር እና ከፋኦ (FAO) ጋር በመሆን እየተዘጋጀ መሆኑንም አክለዋል።
ሌላው ዶ/ር ሰለሞን ያነሱት ስለ ሀገር በቀል ወይም ባህላዊ መድኃኒቶች ሲሆን በሀገራችን ከ80 እስከ 85 በመቶ የሚሆነው ጥቅም ላይ እንደሚውል ቢነገርም አሁን ላይ ወደ ገበያ መጥተው በስፋት ጥቅም ላይ እንደዋሉ አንስተዋል።
እነዚህን መድኃኒቶች በስፋት ወደ ገበያ ለማስገባት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ አንድ የእንስሳት መድኃኒት አምራች ብቻ እንደነበር ያነሱት ዶ/ር ሰለሞን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሀገር ውስጥ አምራቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እና አሁን ላይ ወደ አምስት የሚደርሱ አምራቾች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ጥቅምት 11 ቀን 2019 ዓ/ም
@TikvahethMagazine










